አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር እና ተደማጭነትን ለመጨመር የሚያስችሉ የዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ ሥራዎች መከናወናቸው ተገለጸ፡፡
16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ በሩሲያ ካዛን ከተማ ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሚኒስትሮች ልዑካን ቡድን ጋር በመሆን በጉባዔው ላይ ተሳትፈዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በጉባዔው የነበራትን ተሳትፎ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ በጉባዔው ሰፋ ባሉ አጀንዳዎች ላይ ውይይት መካሄዱንና የኢትዮጵያ ልዑክ በጉባዔው ላይ ውጤታማ ተሳትፎ ማድረጉን ገልጸዋል።
በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር፣ ተሰሚነት እና ተደማጭነትን ለመጨመር የሚያስችሉ በርካታ የዲፕሎማሲ ሥራዎች መከናወናቸውንም አመልክተዋል።
በጉባዔው የኢኮኖሚ ትብብሮች፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያን የተመለከቱ ውሳኔዎች መተላለፋቸውንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በውሳኔዎቹ ላይ የራሷን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን የጋራ አቋም ማንጸባረቅ መቻሏንም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት ጋር ውጤታማ የሁለትዮሽ ውይይቶች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ በተለይም የተለያዩ የብሪክስ አጋር ሀገራት አባል ለመሆን የኢትዮጵያን ድጋፍ መጠየቃቸውንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
በሁለትዮሽ ውይይቶቹ ሀገራቱ ኢትዮጵያ በቀጣናው እና በአፍሪካ ያላትን አቋም እንዲሁም መሰረታዊ ጥቅሞቿን በተመለከተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መደረጉን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ባደረጉት ውይይት ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በውይይቱ ሀገራቱ በቀጣይ በትብብር በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይም አቅጣጫ መቀመጡንና የጋራ መግባባት ላይ መደረሱንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለዋል።