Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር በመመለሱ እንቅስቃሴ የሳዑዲ መንግስት ድጋፉን እንደሚያጠናክር ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር ለመመለስ የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ላለው በጎ እርምጃ የሀገሪቱ መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡

በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) ከሳዑዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች አምባሳደር አሊ አብዱራሃማን አልዩሱፍና የውጭ ሀገር ዜጎች ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ዶ/ር መሃመድ አልሸምሪ ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ሙክታር÷ የኢትዮጵያ መንግስት በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ የገቡ ዜጎቹን በመመለስ ረገድ ያሳየውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የኢኮኖሚ ሁኔታን የማሻሻል፣ በህገ-ወጥ ስደት አስከፊነት ላይ ለዜጎች ግንዛቤ የመፍጠር፣ ህገ-ወጥ የሰው አዘዋዋሪ ደላሎችን ለህግ የማቅረብ እና ከሀገር መውጫ ኬላዎች ቁጥጥርን የማጠናከር ስራዎች ላይ ኢትዮጵያ በልዩ ትኩረት እየሰራች እንደሆነ አመልክተዋል።

በዚህና በሌሎች መስኮች ከሳዑዲ የመንግስትና የግል ሴክተሮች ጋር ያለውን ትብብር ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ማስታወቃቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

ሁለቱ የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት በበኩላቸው÷ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ የገቡ ዜጎችን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ በሌሎች ዘርፎች ለሚደረጉ ግንኙነቶች ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ ያለው ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ የመንግስታቸው ፍላጎት መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህን ወገኖች ለመመለስ የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰደ ላለው በጎ እርምጃም የመንግስታቸው ድጋፍ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

Exit mobile version