Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በባሕርዳር ከተማ የወባ በሽታን የመከላከል ንቅናቄ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ባሕር ዳር ከተማ ክልላዊ ጤና ጣቢያ መር ማኅበረሰብ አቀፍ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ንቅናቄ ዛሬ ተጀምሯል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ጋር በመቀናጀት ንቅናቄውን እንዳዘጋጁት ተገልጿል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም በዚህ ወቅት÷ በክልል ደረጃ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከል ጤና ጣቢያ መር የሆነ ማህበረሰብ አቀፍ የአካባቢ ቁጥጥር ስራን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በበኩላቸው÷ንቅናቄው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የወባ በሽታ የስርጭት መጠን በቅድመ መከላከል ተግባር በመቀነስ በኩል ከፍተኛ ድርሻ ያለውና በየሳምንቱ የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለወባ በሽታ ስርጭት ምቹ የሆኑ አካባቢዎች በመለየት እና በማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ በመታገዘ በቅድመ መከላከል ተግባር ለወባ መራቢያ አመቺ የሆኑ ያቆሩ ውሃዎችን ማፋሰስ ፣ ሳር እና ጥሻ ያለባቸውን ቦታዎች ማጨድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በአማራ ክልል እየተባባሰ የመጣውን የወባ ሥርጭት መከላከል እንዲቻል ሕብረተሰቡ ለአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ኢንስቲትዩት ጥሪ አቅርቧል፡፡

ለወባ ሥርጭት መባባስ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ መዳከም በምክንያትነት መጠቀሱን የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

Exit mobile version