Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአየር ንብረት ችግሮችን ለመቅረፍ በማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ላይ የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአየር ንብረት ችግሮችን ለመቅረፍ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ በማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ላይ የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ጠየቁ፡፡

የአፍሪካ ቀንድ የገንዘብ ሚኒስትሮች ከዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ ስብሰባዎች ጎን ለጎን ለ22ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ በዋሽንግተን ዲሲ ተገኝተው ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ እና በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ቪክቶሪያ ኩዋኩዋ በጥምረት
ተመርቷል፡፡

ለቀጣይ ዘላቂ ልማት ወሳኝ በሆኑ የመቋቋሚያ ጉዳዮች እና አዳዲስ የፋይናንስ ዘዴዎች ላይ ያተኮረ ውይይት እንደሆነም ነው የተገለጸው፡፡

በምክክር መድረኩ አዲስ የተሾሙት የኬንያ እና የደቡብ ሱዳን የገንዘብ ሚኒስትሮችን ጨምሮ የአፍሪካ ልማት ባንክ ተወካይ ኔና ንዋቡፎን እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል፡፡

በአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ለውጥ እየጨመሩ ያሉትን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ የፋይናንስ አቅምን ማሳደግ እና ሌሎች አዲስ መፍትሄዎችን አስፈላጊነት በመድረኩ ትኩረት ተደርጓል ነው የተባለው፡፡

አቶ አሕመድ ሺዴ በዚህ ወቅት ፥ ለአየር ንብረት ሁኔታን መላመድና መቋቋም አሁን ያለው የፋይናንስ ደረጃ በቂ አለመሆኑን በመገንዘብ ኢንቨስትመንትን ማስፋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታትም በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ በማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደር ላይ የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በቀጣናው ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ ማምጣት ላይ ትኩረት ያደረጉ የፋይናንስ ጉዳዮችን ለማሳደግ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ምክክሩ መገባደዱም ነው የተነሳው፡፡

በፈረንጆቹ 2019 የተጀመረው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ፥ ከኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳንን ጨምሮ ከአባል ሀገራት ጋር እንደ ቀጠናዊ ውህደት መድረክ ሆኖ ያገለግላል።

ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማስፋፋት በቀዳሚነት ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች እንደ መሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ የንግድ ፣ ኢንቨስትመንት፣ የሰው ሃብት ልማት እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።

Exit mobile version