ጤና

የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ በተቋማቱ ዲጂታል አሰራርን እውን ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል – ዶ/ር መቅደስ ዳባ

By Shambel Mihret

October 24, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና አገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ በተቋማቱ ዲጂታል አሰራርን በሁሉም ደረጃ እውን ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የጤና ኢኖቬሽንና ጥራት የአፈፃፀም ግምገማና የ2017 ዓ.ም የትኩረት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተጠናቋል።

በዚሁ ወቅት ዶክተር መቅደስ÷በተጨባጭ ውጤት የሚለካ፣ የሚቆጥርና ተጠያቂነት ያለበት የጤና ስርዓት ማረጋገጥ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አንስተዋል።

በዘርፉ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ዲጂታል አሰራሮችን በስፋት ስራ ላይ ለማዋል ትኩረት መደረጉንም ነው የገለጹትገ።

የጤና አገልግሎት ጥራትና ፍትሃዊነት የሚረጋገጠው አሰራሮችና አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ መምራት ሲቻል መሆኑን በመግለጽ የዘርፉ አመራሮች ፈጠራ የታከለበት አዳዲስ አሰራሮችን መተግበር፣ የቁጥጥርና የመለኪያ ደረጃዎች ማስቀመጥ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የጤና ስርዓት አቅም ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በበኩላቸው÷ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ለጤና ኢኖቬሽን፣ ጥራትና ደህንነት እንዲሁም ፍትሃዊ ተደራሽነት መረጋገጥ የተሻለ አስተዋፅኦ ላደረጉና እያደረጉ ላሉ አጋር አካላትና ተቋማት እንዲሁም ሙያተኞች ዕውቅና ተሰጥቷል።