የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ እና አንጎላ የዲፕሎማሲያዊ እና የትብብር ግንኙነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ

By amele Demisew

October 24, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና አንጎላ መካከል የነበሩ የዲፕሎማሲያዊና የትብብር ግንኙነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአንጎላ የውጭ መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ማቲያስ በርቲንዶ ማቶንዳ ገለጹ፡፡

በአንጎላ የውጭ መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ማቲያስ በርቲንዶ ማቶንዳ የተመራ ልዑክ ለሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ፥ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይቷል፡፡

በዚህም ሁለቱ ወገኖች በደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት እና የነበሩ ትብብሮችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችል ምክክር አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም በተቋማት በሚከናወኑ የሁለትዮሽና ሀገራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በስፋት መወያየታቸውን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመልክቷል።

የቀይ ባሕር እና የኤደን ባህረ-ሠላጤ ወቅታዊ ሁኔታዎች፣ በምስራቅ፣ ማዕከላዊ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና የሚንቀሳቀሱ ሽብርተኛ ቡድኖች፣ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይም ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

በተለይም መነሻቸውን ከአንጎላ ሉዋንዳ በማድረግ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚሸጋገሩ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ ለመከላከል እንዲሁም በአቬዬሽን ሴኩሪቲ ዙሪያ በቀጣይ የሚደረጉ ትብብሮችና የመረጃ ልውውጥ መስኮች በውይይቱ ተዳስሰዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል ታዜር ገብረ እግዚአብሔር ÷ ኢትዮጵያ በሠላማዊ አማራጮች የባህር በር ተደራሽነትን ለማግኘት የጀመረቻቸውን እንቅስቃሴዎች ለልዑካን ቡድኑ ገለጻ አድርገዋል፡፡

አንዳንድ አካላት ይህንን ዕውነታ ወደ ጎን በመተው ጉዳዩን ለራሳቸው የፕሮፓጋንዳ ሥራ እየተጠቀሙበት መሆኑን ም አስረድተዋል፡፡

ይህ አካሄድ የአፍሪካ ቀንድና የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን ወደ ቀውስ ሊከት እንደሚችል አብራርተው ÷ የኢትዮጵያ የባሕር በር ተደራሽነት መረጋገጥ ቀጣናውን እንደሚያረጋጋውና ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማምጣት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።

የአንጎላ የውጭ መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ማቲያስ በርቲንዶ ማቶንዳ በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ ካላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት አንፃር ተቋማቸው ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በደኅንነትና ጸጥታ መስኮች የሚያደርገው የልምድና የመረጃ ልውውጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

አምባሳደሩ አክለውም ÷ ኢትዮጵያ በአጭር ዓመታት ውስጥ በዓይን የሚታዩ ታላላቅ የሪፎርም እና የከተማ ልማት ሥራዎችን መስራቷ ለሌሎችም በአብነት የሚወሰድ መሆኑን በመግለጽ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ተቋማት በደኅንነት እና ፀጥታ ጉዳዮች እንዲሁም በመረጃ ልውውጥና ትብብር ሥራዎች አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሠነድ መፈራረማቸው ተገልጿል፡፡