አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ አልባሳት ግዢ ሀሰተኛ የባንክ ዋስትና አቅርቧል የተባለው ስራ አስኪያጅ በሙስና ወንጀል ተከሷል፡፡
ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው፡፡
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳየሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በንግድ ስራ ላይ የተሰማራው ፈይሠል ሻሚል ረዲ በተባለው ተከሳሽ ላይ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 23 ንዑስ አንቀጽ 2 (ሀ) እና ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ የተመለከተውን ድንጋጌ ተላለፏል የሚል ክስ አቅርቦበታል።
በክሱ ላይ እንዳመላከተው ፥ ተከሳሹ የሌላውን ሰው መብት ወይም ጥቅም ለመጉዳት ወይም ለራሱ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሳብ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ በ2016 ዓ.ም ለሰልጣኞችና ለሰራተኞች የሚሆኑ አልባሳትን ለመግዛት በወጣው ግልጽ ጨረታ ተከሳሹ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ የሆነበት ሔልዋ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ብርድ ልብስና ፎጣ ለማቅረብ በጨረታው ተሳትፎ ማሸነፉ በክሱ ተጠቅሷል።
የጨረታ ማስከበሪያ የሚሆን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሚሊተሪ ተራ ቅርንጫፍ ያልተሰጠ በየካቲት 27 ቀን 2016 ዓ.ም በሚል የተጠቀሰ የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና 700 ሺህ ብር ብቻ የሚል ሀሰተኛ የባንክ ዋስትና የሆነ ይዞ መቅረቡ በክሱ ተጠቅሷል።
ተከሳሹ ባቀረበው ሀሰተኛ የባንክ ዋስትናን መነሻ አድርጎ ውል በመዋዋል ጥራቱ ያልጠበቀ ብርድልብስና ፎጣ በማቅረቡ ምክንያት የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ተከሳሹ ያቀረበው የባንክ ዋስትና 700 ሺህ ብር ታግዶ ወደ ዩኒቨርሲቲው የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ እንዲደረግለት ለንግድ ባንክ ሚሊተሪ ተራ ቅርንጫፍ ሲጠይቅ ተከሳሽ ያቀረበው ዋስትና ከባንኩ ያልተሰጠ መሆኑ ከባንኩ መግለጹን ተከትሎ ገንዘቡን ገቢ ሳይደረግ የቀረ መሆኑ በክስ ዝርዝሩ ተመላክቷል።
በዚህም የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ጥቅም በማሳጣት ጉዳት እንዲደርስ ያደረገ በመሆኑ በዐቃቤ ህግ ክስ ዝርዝር ላይ ተጠቅሶ ሀሰተኛ የሆነ ሰነድ በመገልገል በፈጸመው በሐሰተኛ መንግስታዊ ወይም የህዝባዊ ድርጅት ሰነድ መገልግል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሷል።
ተከሳሹ ዛሬ በዋለው የችሎት ቀጠሮ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ቀርቦ የክስ ዝርዝሩ የደረሰው ሲሆን ፥ ችሎቱ ኬዙን በንባብ አሰምቷል፡፡
ከሳሽ ዐቃቤ ህግ 6 የሰነድ ማስረጃና 3 የምስክር ዝርዝር ከክሱ ጋር አያይዞ አቅርቧል።
ክሱ በንባብ ከተሰማ በኋላ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል ትዕዛዝ በመስጠት ተከሳሹ በክሱ ላይ የክስ መቃወሚያ ካለው ለመጠባበቅ ለጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ/ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ