የሀገር ውስጥ ዜና

በክልሉ በመቶ ቀናት ውስጥ በሁሉም ዘርፎች ስኬት መመዝገቡ ተመላከተ

By Feven Bishaw

October 24, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በ2017 ባለፉት መቶ ቀናት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በሁሉም ዘርፎች ውጤት መመዝገቡን የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ ።

የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሰናይት ሰለሞን÷ ክልሉን የሠላም፣ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ግብ ተጠቀምጦ በተሰራው ስራ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልፀዋል ።

በዚህም በክልሉ የመቶ ቀናት ጉዞ በግብርና ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ፣የእንስሳት ዝሪያን በማሻሻል፣ በሌማት ቱሩፋት ፣በመስኖ ልማት እንዲሁም በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና በሌሎች የልማት ስራዎች ውጤት መመዝገቡን አስታውቀዋል፡፡

ከማህበራዊ ልማት አንፃር በተለይ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የመማሪያ መፅሐፍትን በማዳረስ ረገድ እንዲሁም የ2017 የትምህርት ዘመን አጀመማር ላይ መስተጓጎል እንዳይኖር ለማድረግ የመምህራንን ደመወዝና ጥቅማጥቅም ወቅቱን ጠብቆ እንዲከፈል ለማድረግ በተሰራው ስራ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል ፡፡

በጤና ልማት ዘርፍ ባለፉት ወራት በክልሉ የተከሰተውን የወባ ስርጭት ለመከላከል እና ከህክምና ግብዓት አቅርቦት አንፃርም የሚስተዋለውን ዉስንነት ለመቅረፍ የክትትልና የቁጥጥር ስራ መሰራቱንም አንስተዋል።

በክልሉ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ በርካታ አልሚዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉንና በሌላ በኩልም ግንባታቸው ተጀምሮ የተቋረጡ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለህዝቡ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በአምስት ከተሞች እየተተገበረ ባለው ኮሪደር ልማት ህብረተሰቡን በማሳተፍት በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውንም ገልፀዋል፡፡

በማስተዋል አሰፋ