Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

አፍሪካ በዓለም የኢኮኖሚ አስተዳደር ላይ ፍትሃዊ ተሳትፎ እንዲኖራት መስራት ይገባል – አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ በዓለም የኢኮኖሚ አስተዳደር ላይ ፍትሃዊ ተሳትፎ እንዲኖራት መስራት ይገባል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ፡፡

አምባሳደር ምስጋኑ በብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ጉባዔው የደቡብ ደቡብ ትብብርን ለማጠናከር፣ የምንጋራቸው ግቦችና ራዕዮቻችን ዕድገት ማፋጠን ላይ ለመመካከርና የዓለም አስተዳደር ሪፎርሞች ላይ ያለውን እድገት ለመመልከት ያስችላል ብለዋል፡፡

እንደየደቡብ ግሎባል ሀገርነታችን ሃብቶቻችን በማሰባሰብ፣ አቋማችንን በማስተካከል፣ ዓለም እየተፈተነችባቸው ያሉ ችግሮችን ለመጋፈጥ የመስራት ታሪካዊ ኃላፊነትና እድል አለን ሲሉም ነው ያነሱት፡፡

በዚህም ከዓለም ችግሮች መካከል በተለያዩ ቀጣናዎች እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶችን በመቀነስ የሰው ልጅ ስቃይን ለማስወገድ አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ዘላቂ የልማት ግቦች እንዲሳኩ ለልማት የሚውሉ የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም የእዳ ሸክምን ማቃለል እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን ኢኮኖሚና የገንዘብ ተቋማት ትብብር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ ታምናለች ብለዋል፡፡

ይህንን ለማሳካትና የደቡብ ግሎባል በተለይም አፍሪካ በዓለም የኢኮኖሚ አስተዳደር ላይ ያላትን ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ ለማስፋት በጋራ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ ሃሳባቸውን በአግባቡ እንዲያንጸባርቁ የኮታ ስርዓቱን እንደገና ማየት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የደቡብ ግሎባል ኢኮኖሚን አስመልክቶ የተደረሱ ስምምነቶችን ለመተግበር ጥረት ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመው፤ የደቡብ ደቡብ ትብብር የዓለም ሰላምና ደህንነት፣ ድህነት ቅነሳና የአየር ንብረት ለውጥ ላይ በጎ አስተዋጽዖ ማበርከት የሚያስችል አቅም እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በመሰረት አወቀ

Exit mobile version