የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ከአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ ጋር የ45 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራረመች

By Mikias Ayele

October 24, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ ጋር የ45 ሚሊየን ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራርማለች፡፡

ስምምነቱ የአረንጓዴ የአየር ንብረት ፈንድ በደቡብ ኮሪያ ሶንዶጎ ከተማ ባካሄደው 40ኛ መደበኛ ስብሰባ ወቅት መፈረሙ ነው የተገለፀው፡፡

የድጋፍ ስምምነቱ ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች በታዳሽ ሃይል የሚንቀሳቀስ የንፁህ ውሃ አቅርቦት በመገንባት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የውሃ አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ የሚውል መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በፕሮጀክቱ በድርቅ በተጎዱ የአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ገጠራማ አካባቢዎች በፀሀይ ሃይል የሚሰሩ የውሃ ፓምፖች ይዘረጋሉ የተባለ ሲሆን ይህም በድርቅ ሳቢያ የሚከሰተውን የውሃ እጥረት ችግር ይቀርፋል ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከ355 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ እና የግብርና ምርታማነት እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የፕሮጀክቱ 50 ሚሊየን ዶላር ወጪ አጠቃላይ ገንዘብ የሚተገበረው ፕሮጀክቱ፤ 45 ሚሊየን ዶላር በአረንጓዴ የአየር ንብረት ፈንድ እንዲሁም ቀሪው 5 ሚሊየን ዶላር በኢትዮጵያ መንግስት ይሸፈናል ተብሏል፡፡

የድጋፍ ስምምነቱን በኢትዮጵያ የኮሪያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ እና የአየር ንብረት ፈንድ የኢንቨስትመንት ኦፊሰር ሄነሪ ጎንዛሌዝ በጋራ ተፈራርመውታል፡፡