Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአማራ ክልል የወባ ሥርጭት ለመከላከል የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ላይ ትኩረት እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል እየተባባሰ የመጣውን የወባ ሥርጭት ለመከላከል ህብረተሰቡ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ላይ ትኩረት እንዲያደረግ የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥሪ አቀረበ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ የክልሉን የወባ ሥርጭት ሁኔታ እና መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ በ2017 በጀት ዓመት 1 ሚሊየን 548 ሺህ 955 ሰዎች የወባ ምርመራ ተደርጎላቸዋል ብለዋል።

ከነዚህ መካከል 612 ሺህ 905 ሰዎች በወባ ሲጠቁ የ32 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልጸው፤ በክልሉ ያለው የወባ መገኘት ምጣኔ 38 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱንም ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ የወባ ሕሙማን ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ68 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ገልጸዋል።

ለችግሩ መባባስ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ መዳከም መሆኑን አንስተዋል።

የአካባቢ ቁጥጥሩን ለማጠናከር ጤና ጣቢያ መር ማኅበረሰብ አቀፍ ዘመቻ ጥቅምት 15 ቀን 2017 ዓ.ም በባሕር ዳር እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

በመሆኑም የሃይማኖት አባቶች፣ ተቋማት፣ የሙያ ማኅበራት እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም አጎበርን በአግባቡ መጠቀም፣ የወባ ኬሚካል በተረጨባቸው አካባቢዎች ለ6 ወራት የተረጨውን አካባቢ በተለያዩ ነገሮች እንዳይሸፈን በማድረግ ሊከላከል እንደሚገባ ማሳሰባቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version