Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በአቶ አህመድ ሺዴ የተመራው ልዑክ ከዓለም ባንክ ከፍተኛ ሃላፊዎች ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራው ልዑክ ከዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ጋር ተወያየ።

በዓመታዊው የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ጉባዔ ላይ እየተሳተፈ በሚገኘውን ልዑክ ከገንዘብ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎችም ይገኙበታል።

ልዑኩ በዓለም ባንክ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ቀጠና ምክትል ፕሬዚዳንት ቪክቶሪያ ክዋክዋ እንዲሁም የዓለም ባንክ የገንዘብ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት አኪሂኮ ኒሺዮ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይታቸውም ሁለቱ ወገኖች ኢትዮጵያ ስላካሄደችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም በኢትዮጵያ እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች አሁናዊ ሁኔታን በተመለከተ መክረዋል።

አቶ አህመድ ሺዴ ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን ደሀ ተኮር የሪፎርም ስራዎች ከዳር ለማድረስ ከዓለም ባንክ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደምትሻ አስረድተዋል፡፡

የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንቶች በበኩላቸው፤ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት በኢትዮጵያ የተጀመረውን የፖሊሲ ማሻሻያ ማዕቀፍና የፖለቲካ አመራር አድንቀዋል።

ዓለም ባንክ ሀገሪቱ አካታች እና ሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚ የሚያደርግ ኢኮኖሚ ለመገንባት እያደረገች ያለውን ጥረት እንደሚደግፍም አረጋግጠዋል።

Exit mobile version