ደቡብ ኮሪያ ለዩክሬን የመሳሪያ ድጋፍ ልታደርግ እንደምትችል ገለፀች

By Mikias Ayele

October 24, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሜን ኮሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ወደ ሩሲያ መላኳን ተከትሎ ደቡብ ኮሪያ ለዩክሬን የመሳሪያ ድጋፍ ልታደርግ እንደምትችል የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት አስታወቁ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ዮን ሱክ ዮኤል በሰጡት መግለጫ÷ ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገውን ዘመቻ ለመደገፍ ወታደሮቿን መላኳን ደቡብ ኮሪያ በዝምታ አታልፈውም ብለዋል፡፡

ሰሜን ኮሪያ ወደ ሩሲያ የላከቻቸው ከ3 ሺህ በላይ ወታደሮች በተለያዩ ቦታዎች ስልጠና እየተሰጣችው እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ሰሜን ኮሪያ ታህሳስ መጨረሻ ድረስ ከ10 ሺህ በላይ ወታደሮችን ወደ ሩሲያ ለመላክ ማቀዷንም ተናግረዋል።

የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በሩሲያ ስለመኖራቸው ሞስኮ እና ፒዮንግያንግ እስካሁን የሰጡት ምላሽ አለመኖሩን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

በመሆኑም ሰሜን ኮሪያ ወደ ሩሲያ ወታደሮቿን የምትልክ ከሆነ ደቡብ ኮሪያ ከዩክሬን ጋር ወታደራዊ ትብብር እንደምትፈጥር እና ደህንነቷን ለመጠበቅ አስፈላጊ ወታደራዊ እርምጃዎችን እንደምትወስድ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።