የሀገር ውስጥ ዜና

ሀይድሮ ጂኦሎጂ ጥናት በውሃ አቅርቦትና ጥራት ላይ ለሚከናወኑ ተግባራት እገዛ ያደርጋል – ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)

By Shambel Mihret

October 24, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀይድሮ ጂኦሎጂ ጥናት በውሃ አቅርቦትና ጥራት ላይ ለሚከናወኑ ተግባራት እገዛ ያደርጋል ሲሉ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከቼክ ሪፐብሊክ የልማት አጋር ጋር በሲዳማ ክልል እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦና ጋሞ ዞኖች ላይ በተዘጋጀው የጂኦሎጂና የሃይድሮጂኦሎጂ ካርታ ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)÷ ሀይድሮጂኦሎጂ ለኢትዮጵያ ወሳኝ በመሆኑ ጥናቱ በውሃ አቅርቦትና ጥራት ላይ ለሚከናወኑ ተግባራት እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

በካርታ ዝግጅት ሂደቱ የመረጃ አሰባሰብና አያያዝ ስርዓት ላይ ተጨማሪ ግብአት መገኘቱን ገልጸዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴዔታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር)÷ የከርሰ ምድር የውሃ ሃብት የት ቦታ፣ ምን ያህል መጠንና ጥራት እንዳለ ለማወቅ የጂኦሎጂውን ሁኔታ ማጥናት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የጂኦሎጂካል ጥናት የአዲስ አበባ፣ የአርባ ምንጭና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችን በማሳተፍ በናሙና ደረጃ በሲዳማ ክልል፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦና ጋሞ ዞኖች አካባቢ እንደሚሰራ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።