አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ ግለሰቦች ከ2 ዓመት እስከ 12 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጥተዋል፡፡
በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 525 ንዑስ አንቀፅ 1(ለ) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ ግለሰቦች መቀጣታቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገልጿል።
የፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ እንዳስታወቀው፥ በ2016 በጀት ዓመት በዕፅ ዝውውር ከደረሱ ጥቆማዎች መካከል ጠቅላይ መምሪያው የምርመራ መዝገቦችን በሰውና በሰነድ ማስረጃ አጣርቶ ለዐቃቤ ሕግ ከላከው መዝገቦች ውስጥ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ናቸው ብሎ ውሳኔ አስተላልፎባቸዋል፡፡
በዚህም ቺቡኬ ዳንኤል 12 አመት ፅኑ እስራት እና 4 ሺህ ብር፣ ኢጎር ዲማቶስ ዱትራ 3 ዓመት ከ9 ወር ፅኑ እስራት እና 3 ሺህ ብር፣ ሉዊስ ሚጎል ኮናሮጂ 4 ዓመት ፅኑ እስራት እና 4ሺህ ብር ፣ ኬብሮም ሙንዲሀኪ 4 ዓመት ፅኑ እስራት እና 2 ሺህ ብር፣ ሳንጀብ ሙክርጂ 6 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እና 7 ሺህ ብር፣ ጊርሊዬ አሚ 3 ዓመት ፅኑ እስራት እና 3 ሺህ ብር፣ ሄልቪ አልቫላ 5 አመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እና 5ሺህ ብር፣ ራሄል ለገሰ 3 ዓመት ፅኑ እስራት 3 ሺህ ብር፣ ተስፋነሽ አለንሳ 3 ዓመት ፅኑ እስራት እና 3 ሺህ ብር፣ ፑርናማ ጊታ 5 ዓመት ፅኑ እስራት እና 3 ሺህ ብር፣ ናፈትፓት ኑአመንሮም 4 አመት ከ5 ወር ፅኑ እስራት እና 5 ሺህ ብር፣ ዚቱየትነህ 5 ዓመት ፅኑ እስራት እና 3 ሺህ ብር፣ ማርክ ፖወሊኮወ 5 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እና 5 ሺህ ብር፣ ኢማኑኤል ኡዙቸክው 6 አመት ፅኑ እስራት እና 8 ሺህ ብር፣ ባህሩ ወልዴ 12 ዓመት ፅኑ እስራት፣ አስዋልደረፋይል ሄርና 4 ዓመት ፅኑ እስራት እና 3ሺህ ብር፣ ታምሩ ፍቅሬ 12 ዓመት ፅኑ እስራት እና 4 ሺህ ብር፣ ግሬስ አዋርድር 2 ዓመት ከ9 ወር ፅኑ እስራት እና 3 ሺህ ብር፣ ዜመዬ አዩን 5 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እና 3ሺህ ብር፣ ሞሀመድ ሳሉሞኪላማ 6 ዓመት ፅኑ እስራት እና 5 ሺህ ብር፣ ሩአንደርሰደ ሰመዝ 3 ዓመት ፅኑ እስራት እና 3 ሺህ ብር መቀጮ፣ አሊዬ አቡዋ 4 ዓመት ፅኑ እስራትና 2 ሺህ ብር፣ ቻኒካን ቡናሙኤን 3 ዓመት ፅኑ እስራት እና 3 ሺህ ብር፣ ቱርናማ ጊታ ሳሪ 4 ዓመት ፅኑ እስራት እና 5 ሺህ ብር መቀጮ ናቸው።
የተያዙ ኤግዚቢቶች በዓይነት እና በመጠን በአጠቃላይ 176 ሺህ 881.61ግራም ኮኬን፣ 924 ሺህ 450 ግራም ካናቢስ፣ 32 ሺህ 100.89 ግራም ሄሮይን፣ 5 ሺህ 89 ግራም ሄሮይን እና ሞርፊም መሆናቸው ታውቋል።
ግለሰቦቹ ዕፁን ለማዘዋወር የሚጠቀሙባቸው መንገዶች በሆድ/በሰው አካል ውስጥ/በማህፀን/ ኮንዶም በመጠቀም፣ በሻንጣ ውስጥ፣ በጫማ ሶል፣ ወፍራም ልብስ በማስመሰል በመልበስ፣ በተለያየ የመኪና አካል ውስጥ፣ በሻንጣ መጎተቻ ብረት ውስጥ በመበየድ እንደሆነ የወንጀል ምርመራ ቡድኑ አረጋግጧል።
የዕፅ የአዘዋዋሪዎቹ ግለሰቦች የኢትዮጵያን ጨምሮ የናይጀሪያ፣ ብራዚል፣ ታይላንድ፣ አንጎላ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቬንዙዌላ፣ ቤኒን፣ ካሜሩን፣ ናሚቢያ፣ ኮንጎ፣ ኡጋንዳ፣ ኬኒያ፣ ቦሊቪያ፣ ፖላንድ፣ ጀርመን፣ ሴንትራል አፍሪካ፣ ህንድ፣ ቱኒዚያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ማላዊ፣ ጅቡቲ፣ ካናዳ፣ ሞዛምቢክ እና ቱርክዬ ዜጎች መሆናቸውም ታውቋል።
የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋወሪዎቹ መነሻ ብራዚል (ሳኦፖሎ)፣ ደቡብ አፍሪካ (ጆሃንስበርግ)፣ አዲስ አበባ፣ አንጎላ ታንዛኒያ፣ ኬኒያ እና ሌሎች ሀገራት ሲሆን፥ መዳረሻቸው ደግሞ ናይጄሪያ (ሌጎስ)፣ ደቡብ አፍሪካ (ጆሃንስበርግ)፣ ሕንድ፣ ዱባይ፣ አዲስ አበባ እና ታይላንድ ናቸው።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ችሎት 24 የምርመራ መዝገቦችን መርምሮ በሕግ የተከለከሉ ዕጾችን የማዘዋወር ወንጀል የፈፀሙ ተከሳሾችን ያርማል፤ ሌሎችን ያስተምራል በማለት ከ2 ዓመት እስከ 12 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲሁም ከ2 ሺህ ብር እስከ 8 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ወስኖባቸዋል ነው የተባለው።
በተመሳሳይ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በዋሉት ላይም ምርመራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በገጹ አስፍሯል።