Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን የማስተናገድ አቅም አላት – የካፍ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2029 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ አቅም እንዳላት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የቀድሞው የቦትስዋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ማክሊን ኮርቴዝ ሌትሺዊቲ ገለጹ።

46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ትናንት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የኢትዮጵያን የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄ እንዲቀበል ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ ተከትሎ ማክሊን ኮርቴዝ ሌትሺዊቲ እንዳሉት ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2029 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ አቅም አላት፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ ማስተናገድ ጥያቄ በካፍ አሠራር የሚታይ ቢሆንም ኢትዮጵያ አኅጉራዊውን ሁነት የማዘጋጀት የቅድሚያ ዕድል እንደምታገኝ ጥርጥር የለኝም ሲሉም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ በእግር ኳሱ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካውም መስክ ለአኅጉራዊው ልማት በቁርጠኝነት የምትሠራ እውነተኛ አፍሪካዊ ሀገር መሆኗንም ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እና የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማኅበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) ምክትል ፕሬዚዳንት አጉስቲኖ ማዱት ፓሬክ በበኩላቸው÷ ላቀረበችው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ብታገኝ ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እና ለካፍ ትልቅ ትርጉም እንዳለው አመላክተዋል፡፡

ሀገሪቷ በእግር ኳስ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ እና አንድነትን መፍጠር እንደምትችልም ገልጸዋል።

Exit mobile version