Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ማዕቀፉ የተፋሰሱን ሀገራት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ተፈፃሚ መሆኑ የተፋሰሱን ሀገራት ፍትሐዊ የውኃ ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ ተመላከተ፡፡

የውኃ ኃብት ተመራማሪና ባለሙያ ፈቅ አሕመድ ነጋሽ እንዳሉት የስምምነት ማዕቀፉ ዓላማ÷ ዓለም አቀፍ የውኃ ሕግ መርሆዎችን መሰረት ያደረገ፣ ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውኃ አጠቃቀም ማስፈን፣ ቀጣናዊ ትብብር ማጠናከር እንዲሁም ጉልህ ጉዳትን ማስቀረት ነው።

የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የቅኝ ግዛት ስምምነትን የሻረና ፍትሐዊ የውኃ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ መሆኑንም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የቅኝ ግዛት ስምምነቱ የውኃ አመንጪ ሀገራትን ታዛቢ ያደረገ፣ በውኃው ምንጭነት ምንም አስተዋጽኦ የሌላቸውን ሀገራት ፍትሐዊነት በጎደለው መልኩ ተጠቃሚ አድርጎ መቆየቱንም አውስተዋል፡፡

በመሆኑም የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የተፋሰሱን ሀገራት ፍትሐዊ የውኃ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ነው ያሉት፡፡

የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን ያጸደቁ ሀገራት በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል እና በኃብት አጠቃቀም ዙሪያ በትብብር እንዲሠሩ የሚያደርግ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የናይል ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ከጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ተፈጻሚነት መግባቱ ይታወሳል።

Exit mobile version