የሀገር ውስጥ ዜና

ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ተገኘ

By ዮሐንስ ደርበው

October 23, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ሦስት ወራት ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሦስት ወራት 6 ሺህ 456 ጊጋ ዋት ሠዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለሀገር ውስጥ ፍጆታና ለጎረቤት ሀገራት ማቅረብ መቻሉን የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ተናግረዋል።

31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ገቢ የተገነውም ለጅቡቲ፣ ሱዳን እና ኬኒያ 497 ነጥብ 8 ጊጋ ዋት ሠዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወደ ኬንያ ሲቀርብ የነበረው ኃይል በሙከራ ሽያጭ ደረጃ እንደነበር አስታውሰው÷ አሁን ላይ ስምምነቱ በሚያስቀምጠው መሠረት 200 ሜጋ ዋት ኃይል ለሀገሪቱ እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ ለታንዛኒያ እና ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ለታንዛኒያ ኃይል ለማቅረብ ድርድሮች መጠናቀቃቸውን ጠቅሰው÷ ከደቡብ ሱዳን ጋርም የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሞ ቴክኒካል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል፡፡