የሀገር ውስጥ ዜና

ብሪክስ  ባለብዙ ወገን የዓለም ስርዓትን የሚያረጋግጥ ተቋም ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)

By Mikias Ayele

October 23, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሪክስ ባለብዙ ወገን የዓለም ስርዓትን የሚያረጋግጥ የበየነ መንግስታት ተቋም ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሩሲያ ካዛን ከተማ እየተካሄደ ባለው 16ኛው የብሪክስ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ስብሰባው የባለብዙ ወገን የዓለም ስርዓትን ተግባራዊ በማድረግ ሀገራት የሚያጋጥማቸውን ችግሮች መፍታት የሚችሉበት ተስፋ መኖሩን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አዲስ የብሪክስ አባል እንደመሆኗ በፍትሃዊነት መርህ ያደጉ እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ያማከለ ባለብዙ ወገን ትብብር እንዲጎለብት ለማድረግ ትሰራለች ብለዋል፡፡

ዓለማችን የባለብዙ ወገን ትብብሮችን በሚፈልጉ በርካታ ቀውሶች ውስጥ እያለፈች መሆኗን ጠቅሰው÷ በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት እድገት ፍትሃዊ ባልሆነ የዓለም የፋይናንስ ሥርዓት ምክንያት እየተፈተነ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ውስጥ ያለው አለመመጣጠን በታዳጊ ሀገራት ላይ የኢኮኖሚ ልዩነት፣ የዋጋ ግሽበት እና ስራ አጥነት እንዲከሰት እያደረገ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ ዓለምን እየፈተናት ቢገኘም ለአየር ንብረት ፋይናንስ እና እርምጃዎች የቀረቡ ጥያቄዎች ግን እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡