Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የድሬዳዋ አስተዳደር የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት መተግበሪያ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የድሬዳዋ ስራ አስኪያጅ ፅህፈት ቤት እና የአስተዳደሩ ተቋማት የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ለማስጀመር ከ6 ተቋራጮች ጋር ተፈራርመዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የድሬዳዋ ከተማ ስራ አስኪያጅ ፅ/ቤት ኃላፊ ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂም÷ ድሬዳዋን ፅዱና ውብ ከተማ ለማድረግ የሚያስችል የኮሪደር ልማት የቅድመ ዝግጅት ስራ ተጠናቋል ብለዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ጥናትና ዲዛይን የአስተዳደሩና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች በጋራ በመሆን የአዲስ አበባና የሌሎች ከተሞችን ተሞክሮ ቀምረው ከአስተዳደሩ ታሪክና ቅርስ ጋር በሚስማማ መንገድ ማጠናቀቃቸውን አንስተዋል።

በዚህም የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ለማስጀመር ዛሬ ከስድስት ተቋራጮች ጋር የስራ ውል ተፈርሟል ብለዋል።

የከተማው የኮሪደር ልማት የመጀመሪያው ምዕራፍ ከሰብሪያ ሎጅ እስከ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲሁም ከነምበር ዋን እስከ ምድር ባቡር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የስራ ኃላፊነቱን የተረከቡት ተቋራጮች በ90 ቀናት ውስጥ ፕሮጀክቱን በጥራት አጠናቀው ማስረከብ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የአስተዳደሩ የግንባታ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን ጀንበሬ በበኩላቸው÷ፕሮጀክቱ በርካታ ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል የሚፈጠር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ፕሮጀክቱን ለመገንባት ስምምነት ያደረጉ ተቋራጮችም የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version