የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በጂ 24 የገንዘብ ሚኒስትሮችና የባንክ ገዥዎች ስብሰባ እየተሳተፈች ነው

By ዮሐንስ ደርበው

October 23, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዓመታዊ ጉባዔ ጎን ለጎን እየተካሄደ ባለው የጂ24 የገንዘብ ሚኒስትሮችና የባንክ ገዥዎች ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ እየተካፈለች ነው።

በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የተመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑክ በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ባንክ እና አይ ኤምኤፍ ዓመታዊ ጉባዔ ላይ መሳተፉ ይታወቃል።

ልዑኩ ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ የብሪተን ጉድስ ስርዓት ላይ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም አስረድቷል።

አቶ አሕመድ ሀገራት ቀውስ ባጋጠማቸው ጊዜ እሴታቸውን በቀላሉ ወደ ገንዘብ ለመቀየር ፈጣን አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ ስለመሆኑም ገለጻ አድርገዋል።

እንዲሁም ታዳጊ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት በተመጣጣኝ ወለድ የዕዳ ጫና ሳይፈጠርባቸው አስፈላጊ ሀብት ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ሀገራት ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ከግምት ውስጥ ያስገባ በቂ ገንዘብ ማግኘት እንዲችሉና ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ የዓለም ባንክ እና አይ ኤምኤፍ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ድጋፍና ወዳጅነት አድንቀው፤ ይህም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ዕድገት እያገዘ እንደሚገኝ መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።