አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የእስራኤል መሪዎች በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ለማድረግ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ብሊንከን የእስራኤል-ሀማስ ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ 11ኛውን የመካከለኛው ምስራቅ ጉዞ እንዲሁም እስራኤል ከሂዝቦላህ ጋር የነበራት ግጭት ከተባባሰ ወዲህ የመጀመሪያቸው የሆነውን ጉዞ አድርገው ከእስራኤል መሪዎች ጋር መክረዋል።
በውይይታቸውም፥ ባለፈው ሣምንት የእስራኤል መከላከያ ሃይል የሀማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ላይ የፈፀመው ግድያ ለእርቅና በቡድኑ የተያዙ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ዕድል እንደፈጠረ ብሊንከን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ባደረጉት ውይይት ብሊንከን ፥ ወደተከበበው የፍልስጤም ግዛት ተጨማሪ እርዳታ ይፈቀድ ሲሉ ግፊት ማድረጋቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስን ጠቅሶ የዘገበው ገልፍ ቱደይ ነው፡፡
የአሜሪካ አንድ ባለስልጣንም፥ ኔታንያሁ የብሊንከንን እርዳታ ወደ ጋዛ ማድረስ ላይ የሰጡትን ሃሳብ “ከባድነት” ተገንዝበው እንደነበር ገልጸው፥ ሆኖም ወሳኙ የሚተገበረው ውሳኔ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ዋሽንግተን እስራኤል በአካባቢው ያለውን የሰብዓዊ አገልግሎት በፍጥነት ካላሻሻለች ወታደራዊ ድጋፏን ልታቆም እንደምትችል አስጠንቅቃለችም ተብሏል።
ባለስልጣኑ አክለውም፥ ኔታንያሁ ሀገራቸው ሰሜናዊ ጋዛን በረሃብ ለማጥፋት እየሰራች ነው የሚለውን አባባል አስተባብለዋል ብለዋል፡፡
ብሊንከን ከእስራኤል ጉብኝታቸው በኋላ ሳዑዲ አረቢያን እንደሚጎበኙም ተጠቁሟል፡፡