Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ የጸጥታና የደህንነት ተቋማትን እምርታ በማረጋገጥ ላይ ናት – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የጸጥታ እና የደህንነት ተቋማትን እምርታ በማረጋገጥ ላይ መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራርና አባላት እንዲሁም ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የጽሕፈት ቤቶች አመራሮች የሚሰጠው ስልጠና ቀጥሏል፡፡

በዛሬው ዕለት የ”ጸጥታና ደህንነት እመርታ” በሚል መሪ ሃሳብ ገለጻ ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ÷ ኢትዮጵያ የጸጥታ እና የደህንነት ተቋማትን በመገንባት ረገድ የረጅም ጊዜ ባለ ታሪክ መሆኗን አውስተዋል።

እነዚህ ተቋማት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ እንደ ኮሪያ፣ ኮንጎ እና በሌሎች ሀገራት በመሰማራት ሰላም የማስከበር ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን መወጣት መቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ወቅቱን በሚመጥን መልኩ በጸጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ የሪፎርም ሥራ በመሥራት ከፍተኛ አቅም መፍጠር መቻሉን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ዘመኑ የኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ የበላይነት ፉክክር የሚታይበት ብቻ ሳይሆን የጦርነት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ስለሆነም ኢትዮጵያ ከየትኛውም አካል የሚሰነዘርባትን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል የራሷን የፀጥታና ደህንነት ተቋማትን የመገንባትና በሪፎርም የማጠናከር ሥራ ሠርታለች፤ ትሰራለችም ሲሉ አስገንዝበዋል።

መከላከያን ጨምሮ በፀጥታ ተቋማት፣ በኢትዮጵያ የመረጃና ደህንነት፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት እና በፋይናንስ ደህንነት የተጠናከረ የሪፎርም ሥራ ተከናውኗል ማለታቸውንም የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version