ስፓርት

በኢትዮጵያ የወጣቶች ማዕከላት ዓላማቸውን እንዲያሳኩ የፊፋ ድጋፍ ተጠየቀ

By Shambel Mihret

October 23, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት በተሟላ መልኩ አገልግሎት መስጠትና የተቋቋሙበትን ዓላማ እንዲያሳኩ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ከአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) ስራ አስፈፃሚ አባል ኢሻ ጆሃንሰን ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ ስፖርት በተለይም እግር ኳስ በአካል የዳበረ፣ ጤናማና አምራች ዜጋ ለማፍራት ባለው ሚና፣ በዘርፉ የአፍሪካ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶችን ማብቃትና መደገፍ እንዲሁም በቀጣይ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭትን መከላከልና የጤና አገልግሎት ተደራሸነትን ማሳደግን ጨምሮ በሌሎች የትብብር መስኮች አጋርነትን ማጠናከር በሚያስችሉ ነጥቦች ላይም ተወያይተዋል፡፡

ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት÷ በኢትዮጵያ የወጣቶች ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት በተሟላ መልኩ አገልግሎት መስጠትና የተቋቋሙበትንም ዓላማ ማሳካት እንዲችሉ ድጋፍ በማድረግ ፊፋ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

የካፍ ስራ አስፈፃሚ አባል ኢሻ ጆሃንሰን በበኩላቸው÷ ስፖርት የዜጎችን ትስስር ለማጠናከርና የማህበረሰብ ለውጥን ለማፋጠን ትልቅ መሣሪያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ሴቶች ላይ የሚደርሰውን የጤና ችግር ለመቅረፍ “ፒንክ ቻሪቲ ፋውንዴሸ” የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት በማቋቋም የግንዛቤና ንቅናቄ ስራ ሲሰራ መቆየቱ ተጠቅሷል።

በቀጣይም የባለብዙ ወገን ትብብርን በይበልጥ ማጠናከርና ማሳደግ እንደሚገባ በውይይቱ ወቅት መገለጹን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡