አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ እና በሀገሪቱ ገበያ ምርታቸውን በስፋት ለማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
በብሪክስ ጉባዔ ለመሳተፍ ሩሲያ ካዛን ከተማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ልዑክ ከሩሲያ ታታርስታን ግዛት ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ጋር የቢዝነስ ፎረም አካሂዷል።
በፎረሙ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ለዘመናት የዘለቀውን ወዳጅነቷን በይበልጥ በኢኮኖሚ ማጠናከር እንደምትፈልግ አስረድተዋል፡፡
ብሪክስ ይዞት የመጣውን ዕድል በመጠቀም ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን የኢንቨስትመንት እና የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የታታርስታ ግዛት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኢንዱስትሪ እና ንግድ ሚኒስትር ኦሌግ ኮሮብቼንኮ በበኩላቸው፥ የግዛቱ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡
ግዛቷ በግብርና፣ ኢንዱስትሪ እና ሮቦቲክስ ዘርፍ ያላትን ከፍተኛ አቅም ወደ ኢትዮጵያ ማስፋት እንደምትፈልግ አረጋግጠዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሰሐ ይታገሱም (ዶ/ር) ለኩባንያዎቹ ስለ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሪፎርም፣ ቅድሚያ ስለሚሰጣቸው የኢንቨስትመት መስኮች እና ስለተዘጋጁ ማበረታቻዎች ገለጻ አድርገዋል።
የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የሩሲያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ቢሰማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡
የኩባንያ ኃላፊዎቹም በኢትዮጵያ መሰማራት እንደሚፈልጉ አስታውቀው፥ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ልዑክ እንደሚልኩ አመላክተዋል፡፡
በብሪክስ ጉባዔ ለመሳተፍ ሩሲያ ካዛን የሚገኘው የኢትዮጵያ ልዑክ የተለያዩ ኩባንያዎችን ጎብኝቷል፡፡
በአላዛር ታደለ