የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ አደም ፋራህ ከቻይናው ኮሙኒስት ፓርቲ ተወካይ እና ከሀገሪቱ ምክትል ትምህርት ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

By amele Demisew

October 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ከቻይናው ኮሙኒስት ፓርቲ ተወካይ እና ከሀገሪቱ ምክትል ትምህርት ሚኒስትር ዉ ያንና ልዑካን ቡድናቸው ጋር ተወያዩ።

በውይይታቸውም ሁለቱ ወገኖች በፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት ብሎም በሁለቱም ሀገራት በተመዘገቡ የለውጥ ስራዎች ላይ መክረዋል።

አቶ አደም ፋራህ በዚህ ወቅት ÷እየጎለበተ የመጣው የሁለቱ ፓርቲዎች ወዳጅነት እና ስትራቴጂካዊ አጋርነት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ እየተገበረች ላለው ሁሉን አቀፍ ሪፎርም ስኬታማነት የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን አስታውሰው፤ የትምህርት ዘርፉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በፓርቲው የሚመራው የቻይና መንግስት በተለይም በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና እንዲሁም የነጻ ትምህርት ዕድል በመስጠት በአቅም ግንባታ ስራዎች ላይ ለተጫወተው ቁልፍ ሚና ዕውቅና ችረዋል።

ይህም የሁለቱን ፓርቲዎች ስትራቴጂካዊ አጋርነት እና ትብብር ፍሬያማነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቻይና ምክትል ትምህርት ሚኒስትር እና የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ተወካይ ዉ ያን በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያን ሁነኛ እና ስትራቴጂካዊ አጋር ሀገር አድርገን እንቀጥላለን ብለዋል።

የሁለቱ ፓርቲዎች ጠንካራ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰው፤ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ለተመዘገበው የለውጥ ጉዞና ስኬት የለውጡ አመራር ያሳየውን ቁርጠኝነትም አድንቀዋል።

የቻይና መንግስት እና ፓርቲያቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የጋራ ዕድገትና ብልጽግና ላይ የተመሰረተ ሁሉን አቀፍ ግንኙነትን ለማጠናከር አበክረው እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡