አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም በባሕር ዳር ከተማ እያከናወናቸው የሚገኙ ፕሮጀክቶች ከተማዋን ለኢንቨስትመንት በይበልጥ ምቹ እንደሚያደርጓት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ገለጹ፡፡
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋን ጨምሮ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኃላፊዎች በከተማዋ የሚከናነውን የኮሪደር ሥራ እና ሌሎች የልማት እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል፡፡
በዚሁ ወቅትም የኮሪደር ልማቱ ከዕቅድ እና ዲዛይን ጀምሮ ከተቋማቸው ጋር በቅንጅት እየተተገበረ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ÷ ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በመናበብ የቴሌኮም መሠረተ- ልማቶች በጥንቃቄ እንዲዘዋወሩ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
የሚነሱ የቴሌኮም መስመሮችም ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ በፋይበር የማዘመን ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
5ኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ (5ጂ)፣ ስማርት ሲቲ እና ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ባሕር ዳር ከተማን ለኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝም እና ለነዋሪዎቿ ምቹ በማድረግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን ይጨምሩላታል ብለዋል፡፡