Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ቅርንጫፉ ከ86 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶች ላይ ቁጥጥር በማድረግ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፍቃድ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ደቡብ ምሥራቅ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ከ86 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶች ላይ ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፍቃድ መስጠቱን አስታወቀ፡፡

ከመድሃኒት መተጨማሪ ከ238 ሺህ ቶን በላይ ምግብ ላይ ቁጥጥር በማድረግ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፍቃድ መስጠቱን ገልጿል።

የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ እንዳለ እንደተናገሩት÷ ፍቃድ የሰጠው አስፈላጊውን የጥራትና የደህንነት ፍተሻ በላቦራቶሪ ጭምር አድርጎ በማረጋገጥ ነው፡፡

በሩብ ዓመቱ ከ15 ሺህ ቶን በላይ የምግብ ጥሬ ዕቃ እና ከ363 ሚሊየን ብር ዋጋ ያላቸው የመድኃኒት ጥሬ ዕቃዎች ላይ አስፈላጊውን ቁጥጥር በማድረግ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የመልቀቂያ ፍቃድ ሰጥቷል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ከ8 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የሕክምና መሣሪያዎችና መገልገያዎች በሩብ ዓመቱ አስፈላጊውን የጥራት መስፈርት ማሟላታቸው በቅርንጫፉ ተረጋግጦ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የመልቀቂያ ፍቃድ መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም አስፈላጊውን መስፈርት ላሟሉ 40 የምግብ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠቱን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን መረጃ ያመላክታል፡፡

የድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን በተለያዩ የምግብ አስመጭ እና አከፋፋይ ድርጅቶች ላይ መከናወኑንና ቁጥራቸው 35 በሚሆኑ ተቋማትም የውስጥ የጥራት ስርዓት እንዲዘረጉ መደረጉም ተገልጿል፡፡

Exit mobile version