የሀገር ውስጥ ዜና

ዳያስፖራው የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በፈጠራቸው ዕድሎች እንዲጠቀም ጥሪ ቀረበ

By Feven Bishaw

October 22, 2024

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ዳያስፖራው የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በፈጠራቸው አዳዲስ ዕድሎች ራሱንና የትውልድ ሀገሩን እንዲጠቀም የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ጥሪ አቀረቡ፡፡

አቶ ማሞ ምህረቱ በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተዘጋጀና ምሁራን፣ ባለሃብቶችና ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም የሀይማኖት አባቶች በተሳተፉበት መድረክ ላይ ተገኝተዋል፡፡

በመድረኩ ላይ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያና በዚሁ ዙሪያ ስለተፈጠሩ አዳዲስ ዕድሎች ለተሳታፊዎች ገለጻ ተሰጥቷል።

በቅርቡ ወደ ትግበራ የገባው ገበያ-መር የውጭ ምንዛሪ ልውውጥ የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ግኝት በእጅጉ መጨመሩ የተገለፀ ሲሆን ÷ እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች ተጠቅሞ የዳያስፖራ ማህበረሰብ በሀገሪቱ የብልፅግና ጉዞ ላይ የራሱን አሻራ እንዲያሳርፍም ጥሪ ቀርቧል።

በመድረኩ አቶ ማሞ ምህረቱ ÷ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም ስራ ኢኮኖሚው በሚፈለገው መጠን እንዳይንቀሳቀስ አስረው የነበሩ አሰራሮች፣ ህጎችና ፖሊሲዎችን መሰረታዊ በሚባል መልኩ የፈታ መሆኑን ገልጸዋል።

የተፈጠሩ እድሎችን ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሊጠቀሙበትና ሀገሪቱን በጋራ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ሊረባበረቡ ይገባል ማለታቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡