Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የተቀናጀ የወንጀል መረጃ ማስተዳደሪያ ሥርዓት ለማልማት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና ፍትሕ ሚኒስቴር የተቀናጀ የወንጀል መረጃ በዘመናዊ መልኩ በማስተዳደር የዲጂታል ሥርዓትን ማልማት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነብርሃን(ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) ተፈራርመዋል።

የውል ስምምነቱ ከወንጀል ጥቆማ እስከ ፍርድ ድረስ ያለውን የተቀናጀ የወንጀል መረጃ በዘመናዊ መልኩ በማስተዳደር የዲጂታል ሥርዓትን ማልማት የሚያስችል ነው ተብሏል።

ይህም በፍትሕ ሥርዓቱ የአገልግሎት አሰጣጥን ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውሳኔ ለመስጠት እንደሚያግዝ ተገልጿል።

በስምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሞባይል መተግበሪያ እና የዲጂታል ቋት እንደሚያለማ ታውቋል።

ዲጂታል የመረጃ ሥርዓቱ አጋዥ የመልዕክት መለዋወጫ ያካተተ በመሆኑ ማህበረሰቡ የተቋሙን ድጋፍና አገልግሎት በዲጂታል አማራጭ በቀላሉ እንዲያገኝ ያስችላልም ነው የተባለው።

በ84 ሚሊየን ብር የሚለማው የተቀናጀ የወንጀል መረጃ ማስተዳደሪያ ሥርዓቱ በአንድ ዓመት እንደሚጠናቀቅ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version