የሀገር ውስጥ ዜና

ብሪክስ ኢትዮጵያ ያላትን ትብብር የምታሰፋበት ምቹ መድረክ ነው – ዘነበ ክንፉ (ፕ/ር)

By ዮሐንስ ደርበው

October 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነቷ ከሌሎች አባል ሀገራት ጋር ጥልቅ ትብብር እንድታደርግ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ዘነበ ክንፉ (ፕ/ር) ገልጸዋል።

በሩሲያ ሞስኮ ውስጥ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች መምህርና በሩሲያ የአፍሪካ ዳያስፖራዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ዘነበ ክንፉ (ፕ/ር) ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነቷ እና ከሌሎች አባል ሀገራት ጋር ያላት ትብብር የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላት ታሪካዊ ግንኙነት ሀገሪቱ የብሪክስ አባልነቷን ከሌሎች አባል ሀገራት ጋር የጠለቀ ትብብር እንድታደርግ ትልቅ እድል ይፈጥራል በማለትም ገልጸዋል።

ከ26 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎች የከፍተኛ ትምህርታቸውን መከታተላቸውን አስታውሰው፤ ይህም በሀገራቱ መካከል ያለውን የሰው ኃይል ልማት የረጅም ጊዜ አጋርነት አጉልቶ ያሳያል።

ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያለማቋረጥ መደጋገፍና ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነታቸውን ማጠናከር መቻላቸውንም ጠቁመዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁለቱ ሀገራት የንግድ፣ ኢኮኖሚ፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነትን ለማሳደግ ትብብር አድርገዋልም ነው ያሉት።

ይህም ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባላት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማስፋት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ የአባልነት ጥቅሟን ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት የምታውልበት እድሎች እንዳሉ ጠቁመዋል።

በብሪክስ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች የምትገኘው ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ መፍጠሩን ገልጸዋል።

በካዛን እየተካሄደ ያለው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ አባላቱ የትብብር ዋና አቅጣጫዎችን እንዲለዩ ጠቃሚ እድሎችን እንደሚፈጥርም እምነታቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ መሳተፋቸው የሀገሪቱን ሁለገብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስትና ባለድርሻ አካላት የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም አቅምን በብቃት በማስተዋወቅ ይህንን መድረክ ሙሉ በሙሉ ለሀገራዊ ፋይዳ ማዋል እንደሚጠበቅባቸው ፕሮፌሰር ዘነበ አስገንዝበዋል።

በወንደሰን አረጋኸኝ