Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተደራሽነቱን እንዲያሰፋ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2018 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኤሌክትሪክ እንዲያገኙ ቃል በተገባላቸው ቀበሌዎች የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲተባበር ተጠየቀ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሽፈራው ተሊላ (ኢ/ር) ጋር በአርባምንጭ ከተማ ተወያይተዋል።

በዚሁ ወቅት ርዕሰ መሥተዳድሩ ስንቀናጅ  ችግሮችን እየለየን የሕብረተሰቡን ጥያቄዎች መመለስ እንችላለን ብለዋል፡፡

ተቋሙ ከዚህ ቀደም የነበረውን አሠራር በማሻሻል ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት አኳያ ለውጥ ማሳየቱንም ጠቅሰዋል፡፡

ዘርፉ ጥያቄ የሚነሳበት በመሆኑ ፍላጎትን እና አቅርቦቱን አጣጥሞ መሄድ ላይ የበለጠ ሊጠናከርና ሊሰፋ እንደሚገባው ማሳሰባቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

በዚሁ መሠረት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ቃል የተገባላቸው የገጠር ቀበሌዎች አካባቢ የሚነሱ የሕብረተሰቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ተቋሙ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ለዚህም የክልሉ መንግሥት አስፋላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚው በበኩላቸው÷ በሕብረተሰቡ ለሚነሱ የመብራት ተደራሽነት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በውጪ ምንዛሪ እንዲሁም በበጀት ማነስ ምክንያት ተቸግረው እንደነበር አስገንዝበዋል፡፡

አሁን ላይ የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት እና ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የሚሠሩ የተለያዩ ሥራዎች መጀመራቸውን አብራርተዋል፡፡

Exit mobile version