የሀገር ውስጥ ዜና

የካፍ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ተጠናቀቀ

By Feven Bishaw

October 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የተካሄደው 46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቅቋል።

በጉባዔው ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴን ጨምሮ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ እና የካፍ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እና የፊፋ ዋና ፀሐፊ ማትያስ ግራፍስትሮም፣ የካፍ አባል አገራት እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች እና የቀጣናዊ እግር ኳስ ማህበራት ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም ሌሎች የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ተሳትሰዋል።

በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ዓመታዊ የስራ አፈጻጸም፣ የበጀት፣ የፋይናንስ፣ የኦዲት እና የተለያዩ የካፍ ኮሚቴዎች ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የጠቅላላ ጉባዔው ሚና፣ የካፍ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዓመታዊ ስብሰባዎችና የካፍ ኤክስፖን ጨምሮ በካፍ መተዳደሪያ ደንብ ላይ የሚገኙ የተለያዩ አንቀጾች ላይም ማሻሻያ ተደርጓል።

የአፍሪካን እግር ኳስ ልማት እና እድገት ማጠናከር፣ አፍሪካ በዓለም እግር ኳስ ያላትን ውጤታማነት ማሳደግ፣ የስፖርት መሰረተ ልማቶች ግንባታ፣ የካፍ አባል አገራት ለእግር ኳስ ልማት የሚመድቡትን የፋይናንስ መጠንን ማሳደግ በጉባዔው የተነሱ ዋና ዋና ሃሳቦች ናቸው ።

በተጨማሪም ስፖርታዊ ጨዋነት፣ ብልሹ አሰራር በማስወገድ መልካም አስተዳደርን ማስፈን እና ዘረኝነትን መከላከል በጉባዔው ላይ የተነሱ ዋንኛ ጉዳዮች መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡