አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የኢትዮጵያን የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄ እንዲቀበል እና እንዲያጸድቅ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጥሪ አቀረቡ።
በአዲስ አበባ እየተካሔደ ባለው 46ኛው የካፍ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ÷ አፍሪካውያን ቤታችሁ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ አሻራ እንዳላትና በፈረንጆቹ 1957 ካፍ ሲመሰረት መስራች ከነበሩ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ እግር ኳስ ያላትን ታሪካዊ ድርሻ ከግምት በማስገባትበፈረንጆቹ 2029 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ጥያቄ ማቅረቧን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ስታዲየሞች እየገነባች መሆኑን ጠቁመው ÷ያሉት ላይም ማሻሻያ እያደረገች እንደምትገኝ አመልክተዋል።
ካፍ የኢትዮጵያን የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄ ተቀብሎ እንዲያጸድቅ ፕሬዚዳንት ታዬ መጠየቃቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡