የሀገር ውስጥ ዜና

ለሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ትግበራ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

By amele Demisew

October 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲን ለመተግበር ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ ተናገሩ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር 5ኛውን ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር አስመልክቶ “ሀገራዊ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲና የባለድርሻ አካላት ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት እያካሄደ ነው።

የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በወቅቱ እንደገለጹት÷ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ የቁልፍ መሰረተ ልማት ደህንነትን ማስጠበቅ የሚያስችል ሰፊ ይዘት ያለው ነው።

የሳይበር ደህንነት ጉዳይ የአንድ ተቋም ብቻ እንዳልሆነ ገልጸው፤ ፖሊሲውን ተግባራዊ በማድረግ የሳይበር ደህንነትን ለማስጠበቅ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አሰገንዝበዋል፡፡

በውይይቱ የሳይበር ደህንነት ፖሊሲ ይዘት ላይ ገለጻ ተደርጎ ቀጣይ ትግበራው ላይ ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝ ኢዜአ ዘግቧል፡፡