የሀገር ውስጥ ዜና

ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአገልግሎት ክፍያ መጠን መሻሻሉን አስታወቀ

By Shambel Mihret

October 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ፣ የሙሉ ዕውቅና እና የሰነድ ማሻሻያ የአገልግሎት ክፍያ መጠን መሻሻሉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

ቦርዱ በሰጠው መግለጫ÷ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባና የሰነድ ማሻሻያ አገልግሎት ክፍያ በምርጫ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ሥነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀፅ 67/4/ሀ-ለ/ የምዝገባ ጥያቄ ያቀረበ ፖለቲካ ፓርቲ እንደሚከፈል እንዲሁም በአንቀጽ 67 (6) የአገልግሎት ክፍያ መጠኑም በቦርዱ የሚወሰን መሆኑን ደንግጓል ብሏል፡፡

አዋጁ በስራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ያለው የምዝገባ ክፍያ መጠን ለሀገር አቀፍ እና ለክልላዊ ፖለቲካ ፓርቲ ጊዜያዊ ሰርተፍኬት ለማግኘት 100 ብር እንደነበር ቦርዱ አስታውሷል፡፡

እንዲሁም ለሙሉ ዕውቅና ለሀገር አቀፍ እና ክልላዊ ፓርቲ 200 ብር እንደነበር በመጥቀስ የተመዘገቡ ፖለቲካ ፓርቲዎች መሰረታዊ ሰነዶቻቸውን በጉባኤ አሻሽለው ሲያቀርቡ 30 ብር የአገልግሎት ክፍያ ሲከፈል ቆይቷል ብሏል፡፡

የክፍያ መጠኑን በየጊዜው መሻሻል እንደሚያስፈልግ ቦርዱ በማመን ከጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ የሚሆን የአገልግሎት የክፍያ ተመን መሻሻሉንም አስታውቋል፡፡

በተሻሻለው የክፍያ ተመን መሰረትም የጊዜያዊ ዕውቅና ክፍያ 15 ሺህ ብር፣ የሙሉ ዕውቅና ክፍያ 30 ሺህ ብር ሲሆን÷ የሰነድ ማሻሻያ ክፍያ ደግሞ 5 ሺህ ብር መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል፡፡