አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክ በአዳዲስ የልማት ትብብር ዘርፎች ላይ የሁለትዮሽ ውይይት አካሄዱ።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠርና የፍራፍሬ እሴት ሰንሰለትን በማስተዋወቅ ረገድ የበፊቱ ማዕቀፎች ከፍተኛ እገዛ እንደነበረው ገልጸዋል፡፡
በዚህም በውሃና መሬት አያያዝ፣ በአመጋገብ፣ በንፅህና አጠባበቅ ስራዎች አቅምን በማሳደግ ረገድ የተደረገው እገዛ በዕውቀት ሽግግር እና የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ በማገዝ ረገድ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቁመዋል፡፡
የቼክ ሪፐብሊክ የልማት ትብብር እና የሰብዓዊ ድጋፍ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ፒተር ጋንዳሎቪች ፥ ቼክ ሪፐብሊክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን መግለጻቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም እ.ኤ.አ ከ2025 እሰከ 2030 የሚተገበረው የመግባቢያ ሰነድ በሦስት ቁልፍ ዘርፎች ማለትም ፥ በግብርና እና ገጠር ልማት፣በሕዝብ አስተዳደር እና ሲቪል ማህበረሰብ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ማህበራዊ ልማት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
ኃላፊዎቹ በውይይታቸው÷በመጪው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ የቼክ ሪፐብሊክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቭላስቲሚል ቫሌክ በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲሱን የመግባቢያ ስምምነት ለመፈረም ተስማምተዋል።