ስፓርት

የካፍ ጉባዔ በኢትዮጵያ መካሄዱ ለእግር ኳሱ መነቃቃት ይፈጥራል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

By ዮሐንስ ደርበው

October 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 46ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በኢትዮጵያ መካሄዱ ለሀገራችን እግር ኳስ መነቃቃት ይፈጥራል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

46ኛው የካፍ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

አቶ ተመስገን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ 46ኛው የካፍ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በኢትዮጵያ መካሄዱ ለሀገራችን እግር ኳስ መነቃቃትን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

አፍሪካን በዓለም ዐደባባይ ያደመቁ የእግር ኳስ ከዋክብቶችም ለጉባዔው በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ጠቁመው÷ ጉባዔው ስኬታማ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

በጉባዔው የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞትሴፔ እና የካፍ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የዓለም አቀፉ የእግር ማኅበር (ፊፋ) ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እና የፊፋ ዋና ፀሐፊ ማትያስ ግራፍስትሮም፣ የካፍ አባል ሀገራት እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች እና የቀጣናዊ እግር ኳስ ማኅበራት ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም ሌሎች የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።