ዓለምአቀፋዊ ዜና

ሂዝቦላህ በሰሜን እስራኤል የሮኬት ጥቃት መፈጸሙን አስታወቀ

By Melaku Gedif

October 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰው የሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን በሰሜን እስራኤል እና ቴል አቪቭ የሮኬት ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል፡፡

ጥቃቱም በአካባቢዎቹ በሚገኙት የእስራኤል ባህር ሃይል ማዕከልና ደህንነት ቢሮ ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

የሮኬት ጥቃቱን ተከትሎም በቴል አቪቭ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን÷ በከተማዋ የማስጠንቀቂያ ደውል እየተሰማ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የእስራኤል መከላከያ ሃይል በበኩሉ÷ በዛሬው ዕለት ጠዋት ሂዝቦላህ 20 የሚደርሱ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል መተኮሱን አስታውቋል፡፡

አብዛኛዎቹ ሮኬቶች መምከናቸውን ገልጾ÷ ይሁን እንጂ በጥቃቱ የደረሰውን ጉዳት ከመግለጽ መቆጠቡን ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል፡፡

በሰሜን እስራኤል የሚገኙ ሆስፒታሎች በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ወታደሮችን እያከሙ መሆኑን ጠቅሰው÷ እስካሁን 16 የቆሰሉ ወታደሮችን እንደተቀበሉ ገልጸዋል፡፡

በአንጻሩ እስራኤል በዛሬው ዕለት በደቡባዊ ቤሩት በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ የ4 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር አስታወቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በቀጣናው ሰላም ዙሪያ ለመምከር በአሁኑ ሰዓት እስራኤል ገብተዋል።

በቆይታቸውም በቀጣናው ተኩስ አቁም እና የታገቱ ዜጎች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር እንደሚመክሩ ተጠቁሟል፡፡