የሀገር ውስጥ ዜና

አይኤምኤፍ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ይበልጥ እንደሚጠናክር አስታወቀ

By ዮሐንስ ደርበው

October 22, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ዕድገት ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትብብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠ፡፡

በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ የተመራ ከፍተኛ ልዑክ ከአይኤምኤፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ጋር በዋሽንግተን ዲሲ ተወያይቷል፡፡

በውይይቱ ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ተክለወልድ አጥናፉ ተሳትፈዋል፡፡

በምክክራቸውም በኢትዮጵያ እየተከናወኑ በሚገኙ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እንዲሁም ከአይኤምኤፍ ጋር በቀጣይ ትኩረት ስለሚደረግባቸው ትብብሮች መወያየታቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል፡፡

በዚሁ ወቅትም አቶ አሕመድ ሺዴ የኢትዮጵያን ዕድገት በተለይም ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ለማጎልበት በሚከናወኑ ተግባራት የአይኤምኤፍ አስተዋጽዖ የጎላ መሆኑን በማንሳት፤ ምስጋና አቅርበዋል።

በሀገሪቱ እየተተገበረ ስለሚገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻም ባደረጉት ገለጻ÷ ኢኮኖሚውን ለማጠናከር፣ ለማዘመን እና ሁሉን አቀፍ እድገት ለማስፈን ያለመ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ይህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጭነት ወደ ትግበራ ምዕራፍ መሸጋገሩን ጠቅሰው÷ በማክሮ ኢኮኖሚው ዘርፍ ያለውን ጉድለት መቅረፍን ጨምሮ ለዘርፉ ዕድገት ሌሎች አዎንታዊ ሚናዎችን ያበረክታል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑ እና ለዚህም አይኤምኤፍ እውቅና መስጠቱ የተገለጸ ሲሆን÷ ይህም ለሌሎች ሀገራት ጭምር በአርዓያነት ሊወሰድ የሚችል ስኬት መሆኑ ተነስቷል፡፡

በአይኤምኤፍ በኩልም የማስተካከያ ወጪዎችን ጨምሮ የኢትዮጵያን የለውጥ ጥረቶች ለመደገፍ ቁርጠኝነት መኖሩ ተገልጿል፡፡

ሁለቱ ወገኖች ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ዕድገት ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከርም ተስማምተዋል፡፡