Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮጵያ በ2029 የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት አቅም አላት  –  ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ር )

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በ2029 የሚካሄደውን አፍሪካ ዋንጫ የማዘጋጀት አቅም አላት ሲሉ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለካፍ ፣ለፊፋ ፕሬዚዳንቶች እና ለካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከፍተኛ አመራሮች በታላቁ  ቤተ-መንግስት የእራት ግብዣ አከናውነዋል።

በፕሮግራሙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የ2029 አፍሪካ ዋንጫን እንድታዘጋጅ በይፋ ጠይቀዋል።

የካፍ ፕሬዚዳንት  ፓትሪስ ሙትሴፔ በበኩላቸው ÷ በኢትዮጵያ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል  ምስጋና አቅርበው፣ የኢትዮጵያውያን ባህል፣እሴትና እንግዳ ተቀባይነት ኢትዮጵያ  ቤታችን እንደሆነች እንዲሰማን አድርጎናል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የ2029ኙን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ያቀረበችውን ጥያቄ ካፍ ከኮሚቴው ጋር እንደሚመክርበት ገልዋጸል።

የፊፋ ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ÷ የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ የኛም  ሀገር ነች ሲሉ ተናግረዋል።

በመርሐ ግብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለሁለቱም ፕሬዚዳንቶች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን መለያን በስጦታ አበርክተዋል፡፡

በተመሳሳይ የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ 2029 የሚል ፊርማቸውን ያሳረፉበትን ኳስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አበርክተዋል።

 

በፍሬሕይወት ሰፊው

Exit mobile version