አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ አዲስ ክ/ከተማ መርካቶ በተለምዶ ሸማ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን የከተማዋ የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ እንዳሉት÷እሳቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል የእሳት የአደጋ መከላከያ ተሽከርካሪዎችና ባለሞያዎች በስፍራው ተሰማርተዋል፡፡
የእሳት አደጋውን መንስዔና ያደረሰውን ጉዳት ምርመራ ከተጣራ በኋላ እንደሚያሳውቁም ባለሞያው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር የእሳት አደጋና ስጋት መከላከል ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አደጋውን በፍጥነት ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው ጥረት የአካባቢው መንገድ የእሳት አደጋ መኪና በተሟላ ሁኔታ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ በመሆኑ ሄሊኮፕተር ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከንቲባ አዳነች በተከሰተው የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት እጅግ ማዘናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ