Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት በትብብር እንሠራለን- የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራው ውጤታማነትና ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት መሳካት በትብብር እንደሚሠሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አረጋገጡ፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከሁለት ወራት በፊት ወደ ተሟላ ትግበራ መግባቱ ይታወቃል።

የማሻሻያው ዓላማ እና እያስገኛቸው ያሉ ውጤቶች ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም መንግስት በሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሰረት ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መግባቱን ጠቅሰዋል።

በዚህም የዘርፎችን ምርታማነት በማሳደግ፣ የውጭ ሀዋላ ምንዛሪን ከፍ በማድረግ ወርቅና ቡናን ጨምሮ የወጪ ንግድ ገቢን በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመርና ሀገራዊ ገቢን በማሳደግ ተስፋ የሚጣልበት ውጤት ማሳየቱን አብራርተዋል።

በማሻሻያ ትግበራ ሂደቱ በዜጎች ላይ ጫና እንዳይፈጠር የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ረገድ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም ለነዳጅ፣ ለማዳበሪያ፣ ለመሰረታዊ መድሃኒቶች፣ ለዘይትና ሌሎችም ድጎማ የሚሆን ከ328 ቢሊየን ብር በላይ በጀት መመደቡን አንስተዋል።

ከታክስ ገቢ ባለፉት ሦስት ወራት 180 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን ገልጸው÷ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ71 ቢሊየን ብር ብልጫ አለው ነው ያሉት።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚን የመገንባት ግቡን እየመታ መሄዱን አስረድተው÷ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተደረገው ውይይት ዓላማውን በቅጡ በመገንዘብ ለውጤታማነቱ በጋራ ለመረባረብ ነው ብለዋል።

በውይይቱ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ መለሰ ዓለሙ÷ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቋማት የአንድን ሀገር ብልፅግና ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሀገራዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሪፎርም ላይ ትልቅ ሚና እንዳለው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢኮኖሚ እድገት የአንድ ምርጫ ዘመን ስራ አይደለም ያሉት ኃላፊው÷ የረጅም ዓመታት ተከታታይ ዕድገትን የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ÷ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሁሉንም ዜጋ ፍላጎት የሚነካ ብሔራዊ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ገነነ ገረቡ እና የአፋር ሕዝብ ፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ መሀመድ ዳውድ በበኩላቸው÷ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዓመታትን የወሰደ ድርድር በማድረግ አተገባበሩንና ውጤቱን በተመለከተ የተሟላ ግንዛቤ ይዘናል ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው ውጤታማነትና ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት መሳካት በትብብር እንሠራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በስኬት እንዲተገበር መንግስት ጉድለቶችን እየተከታተለ ማስተካከል እንዳለበት አንስተው÷ በእነርሱ በኩል የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

 

Exit mobile version