Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በቀጣዮቹ 10 ቀናት በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዝናብ እንደሚኖር ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በቀጣዮቹ 10 ቀናት በጋ 2ኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ አካባቢዎች ላይ የዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ቀጣይነት እንደሚኖራቸው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ÷ዝናብ ሰጭ የአየር ሁኔታ ክስተት የደቡብና ደቡብ ምስራቅ እንዲሁም በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸው አመልክቷል፡፡

በዚህ መሰረትም የቦረናና ጉጂ ዞኖች፣ የሲዳማ ክልል ዞኖች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች እና የሶማሌ ክልል ደቡባዊ ዞኖች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ዝናብ ቀጣይነት ይኖረዋል ነው የተባለው፡፡

በአሶሳና በማኦኮሞ ልዩ ወረዳ፣ በምዕራብ፣ በምስራቅና ቄለም ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ጅማ፣ ከፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ሸኮና ዳውሮ፣ ማጅንግ ዞን፣በጎፋ፣ ባስኬቶ፣ ደቡብ ኦሞ፤ በኣሊ፣ በአማሮ እና በጌዴኦ እንዲሁም በሲዳማ ክልል አከባቢዎች ላይ በጥቂት ስፍራዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ተገልጿል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ባሌ እና ምስራቅ ባሌ፣ ጉጂና ምዕራብ ጉጂ፣ ቦረና እና ምስራቅ ቦረና ዞኖች፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ፣ ወላይታ፣ ኮንሶ፣ ባስኬቶ እና ቡርጂ ዞኖች ዝናብ እንደሚያገኙም ተጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ ኮንታ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች፣ከሱማሌ ክልል ፋፋን፣ ኤረር፣ ጀረር፣ ኖጎብ፣ ሊበን፣ ቆራሂ ዶሎ፣ ዳዋ፣ ሊበን እና ሸበል ዞኖች፤ እንዲሁም ሀረሪ እና ድሬዳዋ ላይ በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡

እንዲሁም ከክረምት ጀምሮ ዝናብ እያገኙ ባሉት አከባቢዎች ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉዱሩ ወለጋ፣ አርሲ እና ምዕራብ አርሲ፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ፤ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል፣ አሶሳ፣ ካማሺ እና የማኦኮሞ ልዩ ዞን፤ ከጋምቤላ ክልል የኢታንግ ልዩ ዞን፣ ኑዌር፣ አኙዋክ እና ማዣንግ ዞኖች በብዙ ቦታዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡

በሌላ በኩል አልፎ አልፎ ከሚጠናከረው የአየር ሁኔታ ክስተት ላይ በመነሳት ከአማራ ክልል ምዕራብ ሰሜንና ማዕከላዊ ጎንደር፣ ምስራቅ፣ ምዕራብ እና ሰሜን ጎጃም፣ አዊ ዞኖች እና ባህርዳር ዙሪያ፣ በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ዋግኸምራ፣ ሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን ወቅቱን ያልጠበቀ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይ ከትግራይ ክልል የሰሜን ምዕራብ ፣የምዕራብ፣ የደቡብና የደቡብ ምስራቅና ዞኖች፤ ከአፋር ክልል ፋንቲ፣ ማሂ፣ ሃሪ፣ እና ጋቢ ዞኖች፤ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ፣ ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እና ሰላሌ፣ አዲስ አበባ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዞኖች ወቅቱን ያልጠበቀ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ተመላክቷል፡፡

በመሆኑም በሚኖሩት ደረቅ ቀናት የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት መሰጠቱን የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version