ዓለምአቀፋዊ ዜና

እስራኤል በሊባኖስ የባንክ ቅርንጫፎች ላይ ያነጣጠረ የአየር ጥቃት ፈፀመች

By Mikias Ayele

October 21, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እስራኤል ለሂዝቦላህ አገልግሎት ይሰጣሉ ባለቻቸው የባንክ ቅርንጫፎች ላይ ያነጣጠረ የአየር ጥቃት መፈፀሟ ተገለፀ፡፡

በአዲስ የባንክ ኢላማ ጥቃት እስራኤል ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ከ24 በላይ የአየር ጥቃቶች መፈፀሟ ነው የተገለፀው፡፡

ሁለት የአየር ጥቃቶች በቤሩት አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ መፈፀማቸው የተገለፀ ሲሆን በጥቃቱ ወቅት የመንገደኞች አውሮፕላን እያረፈ ነበር ተብሏል፡፡

የእስራኤል መከላከያ ሃይል እንዳስታወቀው÷ በዛሬው የአየር ጥቃት ኢላማ የተደረጉት ባንኮች የሂዝቦላህን እንቅስቃሴን በፋይናንስ የሚደግፉ ናቸው ብሏል፡፡

አል ቃርድ አል ሀሰን የሚል ስያሜ ያላቸው እነዚህ ባንኮች ለሂዝቦላህ የጦር መሳሪያ ግዥ እና ለቡድኑ የወታደራዊ ክንፍ አባላት በቀጥታ ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር ማለቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል ሂዝቦላህ በሰሜናዊ እስራኤል በፈፀመው የአፀፋ የሮኬት ጥቃት ቤየት ሂለል ሞሻቭ በሚባለው አካባቢ የሚገኘውን የእስራኤል ወታደራዊ መሰረት ማጥቃቱ ተገልጿል፡፡

በጎላን ተራሮች በሚገኘው የእስራኤል የጦር መሳሪያ ቤዝ ላይ ቡድኑ ተመሳሳይ ጥቃት መፈፀሙም ተነግሯል።

በተጨማሪም የተቃውሞ እንቅስቃሴ ቡድኑ አይታ አል ሻብ በምትባለው እና የእስራኤል ወታደሮች ሰፍረውባት በነበረችው የሊባኖስ መንደር ላይ የሮኬት ጥቃት መፈፀሙን ፕሬስ ቲቪ ዘግቧል፡፡