የሀገር ውስጥ ዜና

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ጋር የዘመናዊ ፖድካስት ስቱዲዮ ግንባታ ስምምነት ተፈራረመ

By Shambel Mihret

October 21, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በዛሬው ዕለት ከኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ጋር የዘመናዊ ፖድካስት ስቱዲዮ ግንባታ ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው እና የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) ተፈራርመዋል።

በዚሁ ወቅት አቶ አድማሱ ዳምጠው÷ ሀገር በትወልድ፣ ትውልድ ደግሞ በትምህርት የሚገነባ መሆኑን አንስተው ይህም በአንድ ቢሮ ወይንም ተቋም ብቻ እዉን አይሆንም ብለዋል።

በዚህ ረገድ ሚዲያ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን የገለፁት አቶ አድማሱ ፋናም ባለፉት ዓመታት ተወዳዳሪ እና ብቁ ትውልድ በመገንባት ሂደት ውስጥ የራሱን አስተዋፅዖ እያበረከተ ቀጥሏል ብለዋል፡፡

የዛሬው ስምምነትም ከዚሁ ተግባርና ዓላማ ጋር የተቆራኘ መሆኑን የገለፁ ሲሆን÷ፋና መሰል ዘመናዊ ስቱዲዎችን በመገንባት ሰፊ ልምድ ያለው እንደመሆኑ ዛሬ ቢሮው በሰጠን ዕድል ደስተኞች ነን ብለዋል።

ቶላ በሪሶ (ዶ/ር)በበኩላቸው÷”ትልቅ ተሰሚነት፣ ሰፊ ተደራሽነት ካለው እንዲሁም ህዝብን ከሚያስተምርና ከሚያዝናና ትልቅ የሚዲያ ተቋም ጋር በመፈራረማችን ደስተኞች ነን” ብለዋል።

በትምህርት ሴክተሩ ትውልድን ለመቅረፅ ሰፊ የህብረተሰብ ተሳትፎ የሚያስፈልግ እንደመሆኑ ይህን እዉን ለማድረግ ሚዲያ ወሳኝ መሳሪያ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በተለይም ፋና የሚገነባውን ዘመናዊ የፖድካስት ስቱዲዮ በመጠቀም ህብረተሰብን ከመቀስቀስ ባለፈ በተለያዩ ሚዲያዎችና ዘዴዎች የሚተላለፈውን ትምህርታዊ ይዘት አቀናጅቶ ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከዘመናዊ ፖድካስት ስቱዲዮ ግንባታ ከሚያገኘው አጠቃላይ ክፍያ ውስጥ 14 ሚሊየን ብር ያህሉን ለዜግነት አገልግሎት የሚያውል መሆኑን በስምምነቱ ላይ መገለጹን ጠቁመዋል፡፡

የጋራ ስምምነቱ ሁለቱን ተቋማት ይበልጥ የሚያቀራርብ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን÷በስነ- ስርዓቱ ላይ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የአስተዳደር አባላት እንዲሁም የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ አመራሮች ተገኝተዋል።

በመራኦል ከድር