አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር የክብርና የትውልድ አጀንዳቸው መሆኑን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ገለጹ።
መንግሥት ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር በወቅታዊ ሀገራዊና የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አካሂዷል።
በመድረኩ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ÷ የአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታና አንድምታው ላይ ገለፃ አድርገዋል።
በዚህም ዓባይ እና ቀይ ባህር የኃያላን ሽኩቻ ጎልቶ የሚታይባቸው የአፍሪካ ቀንድ ዋነኛ የጂኦ ፖለቲካ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ተለዋዋጭ ቀጣናዊ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ የሚገባትን ብሔራዊ ጥቅም እንድታስጠብቅ ደግሞ እንደሀገር የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያና የጎረቤቶቿ እጣ ፈንታ የተሳሰረ መሆኑን ጠቅሰው÷ የባህር በር የማግኘት ተገቢ ጥያቄያችንም ሀገራዊ መሻታችንን ከቀጣናዊ ትብብር ጋር ያስተሳሰረ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የጥያቄያችንን ተገቢነት በአወንታዊነት ተገንዝቦታል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ አካልን በጋራ በመመከት፣ በቀጣናው ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በመሆኑም የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያን ህልውና እና ጥቅም ለማስጠበቅ በኃላፊነት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ሀገራዊ አንድነትንና ሰላምን ማጠናከር የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነ ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በበኩላቸው፥ የሀገርን ጥቅም ማስከበር የሁላችንም አጀንዳ ነው ብለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባህል ዘርፍ ኃላፊና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት መለሰ ዓለሙ፥ በመድረኩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በወቅታዊ ሀገራዊና ቀጣናዊ ጉዳይ ላይ መግባባት መፍጠራቸውን አንስተዋል።
በተለይም የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ ፍላጎትና ቀጣናዊ ሚና ለማሳካት ብልፅግና ፓርቲ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ በውይይቱ ÷ ቀጣናዊ የጂኦ ፖለቲካ ጉዳይን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ መሰጠቱንና መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት አሰላለፍና የዲፕሎማሲ ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግም ኢትዮጵያ በተለዋዋጭ ሁኔታዎች ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ፍላጎቷን እንድታስከብር በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ መደረሱን አንስተዋል።
አሁናዊ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ትኩረት የሚሻ ነው ያሉት ሰብሳቢው፥ የውስጥ አንድነትን በመፍጠርና ሰላምን በማረጋገጥ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለመሥራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁርጠኝነታቸውን ማረጋገጣቸውንም ጠቅሰዋል።
የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ሰለሞን ታፈሰና የገዳ ስርዓት ለኦሮሞ ነፃነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት አባ ቦኮ ሮበሌ ታደሰ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት በሰላማዊ የዲፕሎማሲ መንገድ እውን እንዲሆን ከመንግሥት ጋር እንሰራለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ሳሙኤል ብርሃኑና የሱማሌ ፌዴራሊስት ፓርቲ ሊቀመንበር ዩሱፍ ሴራደም ከኢትዮጵያ ጥቅም በተፃራሪ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ሴራ ለማክሸፍም የፖለቲካ ልዩነት ሳይገድበን በአንድነት እንሰራለን ነው ያሉት።
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር እና ቀጣናዊ ሚናዋን የማጉላት ጉዳይ የትውልዱ አጀንዳ በመሆኑ የዜግነት ኃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።