የሀገር ውስጥ ዜና

5ኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ ዛሬ በባሕር ዳር ከተማና አካባቢው ጀመረ

By ዮሐንስ ደርበው

October 20, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም በላቀ ፍጥነት የላቀ አገልግሎትን መጠቀም የሚያስችለውን የ5ኛው ትውልድ (5ጂ) የሞባይል ኔትወርክ በሰሜን ምዕራብ ሪጅን ባሕር ዳር ከተማ አስጀምሯል።

በማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬ ሕይወት ታምሩ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን በማድረግ የሀገራችንን እድገት በማሳለጥ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የቴሌኮም አገልግሎት ቀልጣፋና ምቹ መሆን የተፈጥሮ ሃብታችንን በአግባቡ በማሥተዳደርና ኢንቨስት ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ጊዜ 79 ሚሊየን ደንበኞች እንዳሉት ጠቅሰው÷ በተለይም በቴሌብር አገልግሎቱ ባለፉት 3 ዓመታት 50 ሚሊየን አባላትን አፍርቷ ብለዋል፡፡

በዚህም የፋይናንስ አገልግሎቱ አካታች፣ ተደራሽና በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ለማስቻል ተሠርቷል ነው ያሉት፡፡

የ5ኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ጂግጂጋ፣ ድሬዳዋ እና ሐረር ከተሞች ጨምሮ በአካባቢያቸው መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡

የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ እና እርካታን የሚያሳድጉ፣ የአገልግሎት ጥራትን የሚያሻሽሉ፣ ዘመኑ ያፈራቸውን አስተማማኝ አገልግሎቶች ለማቅረብ የሚያስችሉ የቴሌኮም እና ዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በስፋት እየዘረጋን ነው ብለዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 4 ቴሌ እና ጣና አካባቢ፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ (ፖሊ)፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና መ/ቤት እና ድብ አንበሳ ሆቴል አካባቢ፣ ባሕር ዳር ዋና የገበያ ማዕከል፣ አቫንቲ፣ ጃካራንዳና ኩሪፍቱ ሆቴሎች አካባቢያቸው የሚገኙ ደንበኞች የ5ኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ ቴክኖሎጂ ትሩፋት ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል፡፡

እንዲሁም በባሕር ዳር ከተማ የሚገነው አሮጌው አውቶቡስ መናኸሪያ አካባቢዎች የሚገኙ የድርጅት እና ግለሰብ ደንበኞች የ5ኛው ትውልድ የሞባይል ኔትወርክ ቴክኖሎጂ ትሩፋት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

የ5ኛው ትውልድ ቴክኖሎጂ እስከ 10 ጊጋ ባይት በሰከንድ የሚደርስ ከፍተኛ ፍጥነት ያለው ዓለማችን የደረሰበት ዘመናዊ የገመድ አልባ ኔትወርክ ቴክኖሎጂ ሲሆን÷ ዳታ የማስተላለፍ መዘግየትን እጅግ በላቀ ሁኔታ በመቀነስ ረገድ ወደ 1 ሚሊ ሰከንድ የሚያደርስ ቴክኖሎጂ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለስማርት የጤና አገልግሎት እና ለሆስፒታል አስተዳደር፣ ለስማርት ግብርና፣ ለስማርት ትምህርት፣ ለስማርት ማዕድን፣ ለስማርት ማኑፋክቸሪንግ፣ ለስማርት ኤርፖርትና የጉዞ አገልግሎት እና ለስማርት ትራንስፖርት ከፍተኛ አገልግሎት እንዳለው አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ለዘመናዊ የመኖሪያ ቤት፣ ለብሮድካስቲንግና ለመዝናኛ፣ ጌምን ጨምሮ በክላውድ ላይ ለተመሰረቱ የዲጂታል አገልግሎቶች እንዲሁም የሰው ሠራሽ አስተውሎት ትሩፋቶች ለመጠቀም የሚያስችል የቴክኖሎጂ ውጤት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በደሳለኝ ቢራራ