Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚመጥን አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉ እያደገ ያለውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚመጥን አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሠራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው የ100 ቀናት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ትግበራ በሁሉም ዘርፎች አበረታች ውጤት እያመጣ መሆኑ በዚሁ ወቅት ተመላክቷል።

ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷ በዘርፉ የሀገሪቷን የኢኮኖሚ እድገት መሸከም የሚችሉና የሎጂስቲክ አገልግሎቱን የሚያሳልጡ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በሀገሪቱ ተግባራዊ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ሴክተሩ ውጤታማ ሥራዎችን ለማከናወን እንዳስቻለውም ጠቅሰዋል።

ከዚህ ውስጥ ለአርሶ አደሩ በወቅቱ የአፈር ማዳበሪያ ማድረስና ለአምራቹም በቂ የሆነ ግብዓት ለማቅረብ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በሩብ ዓመቱ በሴክተሩ በዋናነት የባሕር፣ የየብስ፣ የአየር ትራንስፖርትን ጨምሮ ደረቅ ወደብን የማልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በተለይ የግብርናው ዘርፍ እድገት እያስመዘገበ በመምጣቱ ይህንኑ የሚመጥን የቀዝቃዛ ምርቶች ማከማቻ የመገንባት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

እየተመዘገበ ካለው የሀገሪቱ እድገት ጋር የሎጂስቲክስ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተካሔዱ ናቸው ብለዋል።

የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማዘመን ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመሆን ግልጸኝነትንና ተጠያቂነትን የሚያሰፍኑ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

አማራጭ የወደብ አገልግሎት ላይም በትኩረት በመሥራት የሀገሪቱ ገቢና ወጪ ንግድ ያለምንም መስተጓጎል እንዲጓጓዝ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለዚህም ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያገናኙ የመንገድ መሰረት-ልማቶችን ከመገንባት አኳያ ኢትዮጵያ የሚጠበቅባትን ተወጥታለች ነው ያሉት፡፡

 

Exit mobile version