የሀገር ውስጥ ዜና

በክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራ 19 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ማዳን ተቻለ

By ዮሐንስ ደርበው

October 20, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትየልማት ተግባራትን በማከናወን 19 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የሚገመት ሀብት ማዳን መቻሉ ተገለጸ፡፡

“በጎነትና አብሮነት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሐሳብ የተከናወኑ የ2016 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የክረምት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማጠቃለያ መርሐ-ግብር በጅማ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በዚሁ ወቅት የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ሙና አሕመድ እንዳሉት÷ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች 52 ነጥብ 7 ሚሊየን የሕብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

በዚህም በመንግሥትና በማሕበረሰቡ ያልተሸፈኑ የልማት ሥራዎችንና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማከናወን 19 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር የሚገመት ሀብት ማዳን ተችሏል ብለዋል፡፡

በ2016 የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም 22 ነጥብ 4 ሚሊየን ወጣቶች መሳተፋቸውንም አንስተዋል፡፡

የበጎ ፈቃድ ሥራው ወጣቹ የየክልሉን ባህል፣ ወግ እና እሴቶችን  እንዲያውቁ  ከማድረጉ ባሻገር÷ እርስ በርስ እንዲተዋወቁና ማኅበራዊ ትስስራቸው እንዲዳብር እድል ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡

የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ማቲዎስ ሰቦቃ በበኩላቸው በክልሉ 9 ነጥብ 8 ሚሊየን ወጣቶች ያከናውኑት የክረምት በጎ ፈቃድ ሥራ÷ 26 ነጥብ 8 ሚሊየን የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል፡፡

በተስፋሁን ከበደ እና አብዱራህማን መሀመድ